Tuesday, April 12, 2016



ቀን 03/08/2008 ዓ.ም

6ኛው ከተማ አቀፍ የትምህርት ፌስቲቫል ተካሄደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ 6ተኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ፌስቲቫል “ጥራት ያለው ትምህርት ለዘላቂ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 29-ሚያዝያ 02/2008 ዓ.ም በዳግማዊ ሚኒሊክ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት በድምቀት አካሄደ፡፡
በፌስቲቫሉ መክፈቻ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማህበራዊ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዲላሞ ኦቶሬ እንዳስታወቁት የትምህርት ፌስቲቫሉ የተሻለ የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር የትምህርት ማህበረሰቡና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማድረግ እንደሚረዳ ገልፀው ፌስቲቫሉ የተማሪዎችን የፈጠራ ችሎታና የምርምር አድማስ በማስፋትና በዚህም ሂደት የተገኙ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ለህብረተሰቡ እንዲሁም ለትምህርት ተቋማት እንዲስፋፉ በማድረግ ለቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚያስችል አስገንዝበዋል፡፡ 
ኃላፊው አክለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ፌስቲቫሉን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በቢሮ ደረጃ ኮሚቴዎችን በማዋቀር የቢሮውን አቅም በማቀናጀትና በተደራጀ መልኩ በመጠቀም ፌስቲቫሉን የተሳካ እንዲሆን ያደረገው ተነሳሽነት አበረታች መሆኑን ጠቅሰው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ለሚሰራቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች መሳካት ሁሉም የትምህርት ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ኃላፊነት ስላለባቸው ብቁ ሀገር ተረካቢ ዜጋ ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሳይንስና ሒሳብ ትምህርት ዘርፍ የተፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ ሁሉም የተጣለበትን ኃላፊነት እንዲወጣ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ፌስቲቫሉ ለአራት ተከታታይ ቀናት ሲካሄድ ከ10ሩ ክፍለ ከተማ የተውጣጡ የልዑካን ቡድኖች የሽብርቅ ስራዎቻቸውን ለዕይታ ያበቁ ሲሆን ከዚህ ጎን ለጎን በተማሪዎች የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች በተለያዩ አካላት እንዲጎበኙ ከመደረጉ ባሻገር ፌስቲቫሉን ምክንያት በማድረግ የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ውድድር፣ ትምህርታዊ አውደ ጥናት እንዲሁም በተማሪዎች መካከል የስነ-ፅሁፍ ውድድሮች ተካሄደዋል፡፡
በፌስቲቫሉ ማጠቃለያ በየዘርፉ አሸናፊ የሆኑ ተማሪዎችና ክፍለ ከተሞች የገንዘብና የዋንጫ ሽልማት የተበረከተላቸው ሲሆን በየትምህርት እርከኑ በተፈጥሮና በማህበራዊ ሳይንስ የፈጠራ ስራ አሸናፊ የሆኑ ተማሪዎች ከ2,500-3,500 ብር ሽልማት ሲያገኙ በፌስቲቫሉ የነቃ ተሳትፎ በማድረግና በአጠቃላይ ውጤት 1ኛ አራዳ 2ኛ ቦሌ እንዲሁም 3ኛ የካ ክፍለ ከተማ በመሆን  የዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
 ዘገባው የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዬች ደጋፊ የሥራ ሂደት ነው፡፡